መንፈሳዊ ሰው ፖለቲካ አያገባውምን?


  መንፈሳዊ ሰው ፖለቲካ አያገባውምን?

  (ዮሴፍ ወርቁ)

                የተወደዳችሁ ወገኖች የክርስትናና የፖለቲካ ግንኙነት ሰፊ በመሆኑ እንዲህ ባጭር የሚነገር አይደለም። ነገር ግን ለመነሻ ያህል ዛሬ በሀገራችን (በሌላ አገርም ቢሆን) እየደረሰ ካለው ችግር አንጻር የተሰማኝ ትንሽ ለመናገር ያህል ነው። በተለይ በክርስትና ስለሌላው ሰው ችግር መናገር መንፈሳዊነትን ስለተላበሰ ሰብአዊነት መናገር እንጂ ስለፖለቲካ መናገር አይደለም። ስለፖለቲካም ቢሆን እኮ ከፖለቲካ ተጽዕኖ ውጭ የሆነ ሰው በአለም ላይ ማንም የለም በምክንኩስናም ቢሆን። ስለሌሎች ደህንነት ማሰብ ከፖለቲካም በላይ መንፈሳዊነት ነው። … በተለይ በዚህ ወቅት በሀገራችን ያለው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እጅግ አስጊ ሆኖ ወሬው ሁሉ በየቀኑ የሞት ብቻ በሆነበት ሰአት ፖለቲካ ነው ብሎ ዝም ማለት ምን ማለት ይሆን? … ዝምታ ካለማወቅ ካለመገንዘብ፥ ወይም ደግሞ እያወቁም ቢሆን በእኔ ላይ እስካልመጣ ድረስ እኔ ስለሌላው ምን-አገባኝነት፥ አሊያም ደግሞ በተደረገው ነገር ከመስማማት ከዚህ ከፍ ሲልም ከፍርሀት የሚመነጭ ካልሆነ በስተቀር ከየት ሊመጣ ይችል ይሆን?
                በርግጥ እንጸልያለን እግዚአብሄር ሁሉንም ይቆጣጠራል ” God is in Control ” ብለን እናምናለን። ነገርግን ሰው በሰው ፈቃድ ውስጥም ስላለ ለእግዚአብሄር (ለጸሎታችን) ብቻ የምንተወው ጉዳይ ብቻ አይደለም። መጽሀፍ ቅዱስ የሰዎች መንፈሳዊ ህይወት ታሪክ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካዊ የማህበራዊና የኢኮኖሚ መስተጋብር ታሪክ ጭምር ነው። ሰው መንፈስ ብቻ ቢሆን ኖሮ በስጋ በዚህች ምድር መኖር ባላስፈገውና እግዚአብሄርም ከመነሻው ሰውን ከአፈርና ከውሀ ባልፈጥረውና በምድር ኑር ባላለው ነበር። ወይም እግዚአብሄር ሰውን መንፈስ ብቻ አድርጎ በፈጥረው ነበር። ሰው መንፈሳዊ ቢሆንም በምድር ላይ በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ ስር የወደቀ ነው።
                ስለሆነም “የተገለጸ ዘለፋ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል” (ምሳሌ 27፡5) እንዲል መጽሀፍ ቅዱስ ተጽእኖውን በተግሳጽ፥ በምክር ደግሞም በመግባባት በፍቅር እንድናሸንፈው እንጂ በሰው ልጆች ላይ ምንም ቢፈጠር ግድ የማይሰጠን ከሆነ መንፈሳውያን የሆንን አይመስለኝም። ሰው ሁሉ ፖለቲከኛ ነው ማለት ሳይሆን እንደጌታ ትዕዛዝ ሰው ሰውን እንደ እራሱ በእውነት የሚወድ ከሆነ ሰለሌላው ሁለንተናዊ /Holistic/ ደህንነት መጨነቅ አለበት ለማለት ነው። ጌታ ” ሰርግ ቤት ከመሄድ ሀዘን ቤት መሄድ ይሻላል”  ሲል ምን ማለቱ ይሆን? እስከ ሞት የሚያደርሰው ችግራቸው ይሰማን ከማለቱ ውጭ። ሰዎችን ከምንረዳባቸው መንገዶች አንዱ በሀሳብ ነው። ይህም በበሚያበረታታ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ወደ እውነት በሚያመጣ በተገለጠ ወቀሳ ጭምር ነው። ይህ ደግሞ መጽሀፍቅዱሳዊ ነው። መንግስት ስህተት ሲሰራ እንዲታረም መናገር ቁጭ ብሎ ከማየት ይበልጣል። በተለይም የሰዎችን ደህንነት ከእግዚአብሄር በታችና በራሱ ሰውኛ ድርሻ ለመጠበቅ ሀላፊነት የወሰደው መንግስት በስህተት ውስጥ ሲወድቅ ሰላምና መግባባት በህዝብና በመንግስት መካከል እንዲመጣ መጣር ያለበት ከማንም በላይ ክርስቲያን ነው። ምክንያቱም ይህም መጽሀፍቅዱሳዊ ስለሆነ ነው።
                በኢትዮጵያ የተለያዩ ስፍራዎች ሰዎች በየቀኑ ይሞታሉ። በቅርቡ በቢሾፍቱ (ደብረዘይት) በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት አደጋ መድረስ እጅግ ልብን የሚያሳዝን ከፍተኛ ሀዘን ነው። ቢሾፍቱ (ደብረዘት) ከተወለድኩባት ከተማ በመቀጠል 2ኛ ደረጃ ትምህርት እስከምጨርስ ያደግሁባት ከተማ ስለሆነች ብቻ ሳይሆን ባንድ ጊዜ የዚህን ያህል ህዝብ በድንገት ያውም በሰው ሰራሽ አደጋ በማለቁ እጅግ እጅግ ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶኛል። … ችግሩ የዚህ አካባቢ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ቀውስ ስለሆነ ከጸሎት በመለስ ዝም ልንል የሚያሰኝ ምንም ምክንያት ያለን አይመስለኝም። ስንት ሰው እስከሚያልቅ ነው ዝም ማለት ያለብን? ስለምን ዝም እንላለን? መፍትሄ በመጠቆም ህዝብንም መንግስትንም አንረዳም? እኛ እስካልተነካን ድረስ ከሆነ ይህስ ክርስቲያናዊነት መንፈሳዊነት ነውን? አይመስለኝም። ስለዚህ መስተካለል ያለበት እንዲስተካከል የሚሰማኝን ቅሬታ በሀሳብ እንኳን ለመርዳት የበኩሌን አልኩ፤ ቢያንስ ቅሬታዬን ገለጽኩ። ሌሎች ክርስቲያኖችም ስሌላው ሰው ችግር ዝም ቢሉ፥ የበኩላቸውን እርዳታ ባያደርጉ ደህንነታቸው ጥያቄ ውስጥ ባይገባም ምናልባትም መንፈሳዊ ግንኙነት /Fellowship/ እንዳይሰምር በማድረግ ተጽእኖ ይመጣ ይሆናል።
እግዚአብሄር ጸጋውንና ሰላሙን ያብዛልን !!!
Posted in ጉዳዮች - Affairs | 2 Comments

Posted in Amharic Blogs, ወግ - Essay, የህይወት ጉዳይ- Spiritual, ጉዳዮች - Affairs, Yosef W. Degefi | Leave a comment

አስባት እናት አገሬን


hj

(ግጥም በደረጀ ከበደ (ዶ/ር))

ካድማስ ማዶ ያለች ምድር የማስባት

እትብቴ ስወለድ የተቀበረባት

በቁጣው በትር ተመታ እያነከሰች

ከሀሳቤስ መች ተለየች

ከጭንቀቴስ መች ተለየች
ከጸሎቴስ መች ተለየች

ቀኑም ቢለዋወጥ ዘመን ቢፈራረቅ

ሮሮዋ ብዙ የእናት አገሬ ጣር

ማነው ነህምያ እሷን የሚጠግን

ሀፍረተ ሥጋዋ እርቃኗ ሳይባክን

ጭጋጉ እስከሚለቅ ድፍርሱ እስኪጠራ

እግዚአብሔር በምሕረት ፊቱን እስኪያበራ

አፈርሽ ረጥቦ መዘናጠል ቀርቶ
ተዋርደሽ ለእግዚአብሔር እጅሽ ተዘርግቶ

ኢትዮጵያ ቀኑ እስከሚደርስ ወደ አምላኬ ላልቅስ

ወደ አባቴ ላልቅስ

አስባት እናት አገሬን

ምህረትህ ከሁሉም በላይ

ሰላምታህ ይምጣ ከሰማይ

ካድማስ ማዶ ያለች ምድር የማስባት
እትብቴ ስወለድ የተቀበረባት

በቁጣው በትር ተመታ እያነከሰች

ከሀሳቤስ መች ተለየች

ከጭንቀቴስ መች ተለየች

ከጸሎቴስ መች ተለየች

የፈረሶች ኮቴ የሠረገላ ድምጽ
የትውልድ ጥፉ በእግዚአብሔር የሚያምጽ

መዘዝ ጎተተባት በግኡዛ ምድር

ቁጥር አልቻለውም የበደሏን በትር

ጭጋጉ እስከሚለቅ ድፍርሱ እስኪጠራ

እግዚአብሔር በምሕረት ፊቱን እስኪያበራ

አፈርሽ ረጥቦ መዘናጠል ቀርቶ
ተዋርደሽ ለእግዚአብሔር እጅሽ ተዘርግቶ

ኢትዮጵያ ቀኑ እስከሚደርስ

ወደ አምላኬ ላልቅስ

ወደ አምላኬ ላልቅስ

አስባት እናት አገሬን

ምህረትህ ከሁሉም በላይ

ሰላምታህ ይምጣ ከሰማይ
ሰላምታህ ይምጣ ከሰማይ

ካድማስ ማዶ ያለች ምድር የማስባት

እትብቴ ስወለድ የተቀበረባት

በቁጣው በትር ተመታ እያነከሰች

ከሀሳቤስ መች ተለየች

ከጭንቀቴስ መች ተለየች

ከጸሎቴስ መች ተለየች
ቁጣው ነደደባት ምድራችን እራደች

እህሉን ባንበጣ ወይራችንን በተምች

ገሞራና ሰዶም ሆናለች ምድሪቱ

በቃሽ በላት ዛሬም ደግ አምላክ አቤቱ

ጭጋጉ እስከሚለቅ ድፍርሱ እስኪጠራ

እግዚአብሔር በምሕረት ፊቱን እስኪያበራ

አፈርሽ ረጥቦ መዘናጠል ቀርቶ

ተዋርደሽ ለእግዚአብሔር እጅሽ ተዘርግቶ

ኢትዮጵያ ቀኑ እስከሚደርስ

ወደ አምላኬ ላልቅስ

ወደ አምላኬ ላልቅስ

አስባት እናት አገሬን

ምህረትህ ከሁሉም በላይ

ሰላምታህ ይምጣ ከሰማይ

ሰላምታህ ይምጣ ከሰማይ

 

 

 

 

Posted in Amharic Blogs, የሰሞኑ ጉዳይ - News, የሳምንቱ ታላቅ ወሬ News ov Z Week, ጉዳዮች - Affairs, The Blogger's Diary | Tagged , , , , , , , | Leave a comment