የአቶ መለስ “ኮምፓስ” . . . የቡና ላይ ወግ . . . (ቶማስ ስብስቤ)


መምሬ አሻግሬ ከሳምንታት በፊት ከማሚቴ የተረከቡትን የሐጂ ሲራጅ ጋቢ  ቋጭተው አልጨረሱም፡፡ በነገራችን ላይ ጋቢው ሲጠናቀቅ፣ የጋቢ ታሪክ ተመራማሪዎች የጋቢውን ህይወት ታሪክ እንዲህ ብለው ባንድ ዓረፍተነገር ሊቋጩ ይችላሉ፡፡

ጋቢውን ማሚቴ ፈተሉት፤ ወላ ሸመኑት፤ መምሬ ቋጩት፤ ሐጂ ለበሱት፡፡ አራት ነጥብ፡፡

ሐጂ ሲራጅ ግንባራቸውን ቋጠር ፈታ እያደረጉ አንድ የግል ጋዜጣ ይዘው ሲያነቡ፣

“ምን እያነበቡ ነው ሐጂ?” አልኳቸው

“አረ ሚገርም ነው ሆሆሆ . . .”

“ምንድነው እሱ?”

“ሱዳንና ግብጽ የህዳሴውን ግድብ በጀት ለማጥቃት እንዳሰቡ ተደረሰባቸው” ይላል፣

“ይኼንማ አዎ ፌስቡክ ላይ አይቼዋለሁ፣ ግን ምንያህል እውነት እንደሆነ እንጃ እንጂ፡፡” አልኩ አንገቴን ወደጋዜጣው እያሰገግኩ

“ለማጥቃት? እንዴት ሆኖ ባክዎ?” መምሬ ቁጨታቸውን እያከረሩ፣

“ዝም ብሎ ነው ያሸባሪዎች ወሬ” ገብሩ እያናናቀ፣

“እንዴት ዝም ብሎ ይባላል፣ ሁሉን መናቅ ጥሩ አይደለም!” ጋሼ ወላ፤ አይኖቻቸው ጥርጣሬ እየረጩ

“ምንኮ የኛ ጋዜጦች የሚያወሩት ወሬ እንዴት ይታመናል ብዬ ነው?”

“አይመጣምን ትተሸ  ይመጣልን አስቢ ነው ነገሩ ፣ ሰው አንዳች ሳይዝ መች ያወራና?” መምሬ ገብሩን እየገረመሙ፤

“ምንነካችሁ የግብጽ መንግሥትኮ በግድቡ መገንባት ተቃውሞ እንደሌለው በተለያዩ ጊዜያት አሳውቋል፡፡ በቅርብ ጊዜ ራሱ ጠቅላይ ሚንስትሩ ታመሙ ታመሙ በተባለበት ጊዜ አባይን በሚመለከት ማንኛውንም ነገር ከሚመጣው አዲስ የመንግሥት አካልጋ የምንነጋገር ይሆናል ሲል አልነበር እንዴ?”

“ኤዲያ እነዚህ ጋዜጦች ሲባሉ ሥራቸው ደርሶ ሰው ማሸበር ነው እንዴ ጎበዝ? ምነው ስንት ሚወራ እያለ፣ ይሄን የሽብር ወሬ ይነዙብናል? ኤዲያልኝ እቴ!” አሉ ማሚቴ ጋዜጣውን በጥላቻ እያዩ

“ይሄኮ የሽብር ወሬ ሳይሆን የተጠንቀቁ ወሬ ነው፤ የሽብር ወሬ የሚባለው ሆነ ተብሎ ፣ ተቀነባብሮ  ያላንዳች መረጃ በሰላም ይኖር የነበረውን ህዝብ የሚያሸብር ወሬ ነው፤ ትዝ ይላችሁ እንደሆነ ያኔ እንደአሸን የፈሉት ጋዜጦች . . .” ስል

“አዎ አዎ በጣም የሚገርምኮነው ገናለገና ነፃ ፕሬስ አለ እየተባለ እንዴት ህዝብን የሚያሸብር ወሬ ይጻፋል?” አለ ገብሩ እየተብከነከነ

“ምናልክ ነፃ ፕሬስ? . . . ቂቂቂቂቂ . . .” ትን እስኪለኝ ሳቅሁ

“ምን ያስቅሃል?”

“ያልከው ነዋ!. . . ፣ ነፃ ፕሬስ፣ እውን ገብሩ አፍህን ሞልተህ ስለነፃ ፕሬስ ስታወራ ትንሽ አይሰቀጥጥህም እንዴ?”

“ኤዲያ ይሄ ቦተሊካችሁን ወዲያ አርጉልኝ፣ ቡናዬን በሰላም ልጠጣበት! ሆሆሆሆ . . .” ማሚቴ ተቆጡ

“ምን ይላል ይሄ? . . .  እነዚያ በኦጋዴን በኩል መንግሥቱ ኃይለማርያም ጦር ይዞ መጣልህ፣ በዚህ እንዲህ ሆነልህ፣ በዚያ እንዲያ ሆነብህ እያሉ የነበሩት ጋዜጦች አይነት ሲፃፍ ነው ነፃ ፕሬስ የምትለው?” አሉ ወላ

“አዎ አሁን እነሱ ጋዜጦች እንዲያ ይጽፉ የነበሩት በመረጃ ተደግፈው ሳይሆን በሰላም ይኖር የነበረውን ህዝብ ለማሸበር ነበር” አለ ገብሩ

“ግንኮ እነሱም የህዝብ አካል ናቸው ፤ አይደለም እንዴ? ” አሉ ሐጂ

“አዎ ግን ጫት ላይ ሆነው በምርቃና ስለሚጽፉ የህዝቡ አካል መሆናቸውን ይረሱታል” ቢል ገብሩ፤  የቡናው ዕድምተኞች በጠቅላላ በሳቅ ጦሽ ብለን ፈነዳን፡፡ ይኼኔ እኔ ጋዜጠኛው ወዳጄ ማቲያስ የነገረኝ አንድ ነገር ትዝ አለኝና፣

“ለነገሩ እኔ እንዲያ ለማለት አልነበረም የፈለኩት፡፡ አንድ ጋዜጠኛ ወዳጅ አለኝ” ስል ሁሉም ከሳቃቸው ጋብ ብለው አፍ አፌን ያዩ ጀመር፣

“ትክክለኛ ሚዛናዊ ጋዜጠኝነት ማለት ከማንም ሳይወግኑ የሚሠሩት ነው፣ አሁን ለምሳሌ ሁለት አካላት ባይስማሙ የራስን ስሜት ሳይደባልቁ፣ የሁለቱንም ትክክለኛ መረጃ መዘገብ ማለት ነው፤ እኛ አገር ግን የመንግሥት የሚባሉት ጋዜጦች ለመንግሥት ዘብ የቆሙ፣ የግሎቹ ደግሞ አጠፋም አለማም፣ መንግሥትን የሚኮንኑ፣ አጠፉም አለሙም ተቃዋሚዎችን  እሰየው! አበጃችሁ! የሚሉ አይነት ነገሮች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ትክክለኛ ና ነፃ ሚዲያ ገና ነው፡፡ እነዚያ ከ97 በፊት የነበሩት ጋዜጦች ግን እንደ ወዳጄ ጋዜጠኛው ማቲያስ “ሴንስሽናል” ነው የሚባሉት፡፡ የሆነ ያልሆነውን እያወሩ ስሜት በመኮርኮር የሚፃፉ ሲሆኑ ዋነኛ ዓላማቸው ብር ነው፡፡ ህዝብ ተሸበረ አልተሸበረ፣ አገር ተናጋ አልተናጋ ጉዳያቸው አይደለም” ስል መምሬ አሻግሬ የዲስኩሩን ኳስ ካፌ ነጥቀው፣

“እውነት ብለሃል ልጄ፣ አሁንለታ ማነው አንድ ጋዜጠኛ በቴሌቢዥን ሲናገር ምናለ፣ ቤተመንግሥት ውስጥ ቦንብ ፈነዳ ካላልን ሕዝቡ ጋዜጣችንን አይገዛም፤ እውነትኮ ነው ታዝባችሁ እንደሆነ ብዙ ጊዜ ከበጎው ይልቅ መጥፎውን ነው ማንበብ የሚቀናን” ብለው ወደ ቁጨታቸው ተመለሱ፤

“አሁን ታዲያ ይህ ጋዜጣ ሚያወራው ውነት ነው? ” አሉ ማሚቴ ሐጂ ወደያዙት ጋዜጣ በፍርሃት እያዩ፣

“ምን ይታወቃል፣ አላህ ብቻ ነው የሚያውቀው ” አሉ ሐጂ

“ለማንኛውም ፌጦ መድሃኒት ነው እንደተባለው ነገሩን መመርመር ነው፤ ወሬው እውነትም ከሆነ ያለፈው መለስ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም” አሉ ወላ ጋዜጣውን እየገላመጡ፤

“ትክክል! ወላድ በድባብ ትሂድ ስንት ጅግና ሞልቷል አገሩን የሚያስከብር፣ ኢትዮጵያ በየዘመኑ የሚነሳ የየጊዜው ጅግና አላት ” አሉ መምሬ አሻግሬ በጣታቸው ከምላሳቸው ጫፍ ምራቅ እየተዋሱ፣

“ትክክል፣ ምንድነው መሰላችሁ መለስ ቢሞት ሐሳቡ አልሞተም፣ ዕቅዱ አልሞተም፣ ዋናው ነገር ያ ነው” አለ ገብሩ

“አይይ አይመስለኝም፣” አልኩ

“እንዴት?”

“ኮምፓሱ ከመለስጋ አብሮ ግብአተ መሬት የወረደ ነው የሚመስለኝ”

“የምኑ ኮምፓስ?”

“አገሪቱ የምትመራበት”

“ሕገመንግሥቱን ማለትህ ነው?”

“አይደለም እሱማ በወረቀት የሰፈረ፣ ወረቀት የያዘው ነው”

“ታዲያ የምን ኮምፓስ ነው ምታወራው ያለህ?”

“መለስ በልቡ ውስጥ ያለ የራሱ የሆነ፣ የተፈጥሮ የአመራር ስልቱ፣ ብልሃቱ፣ ለዘመናት በረሃ ላይ ያከማቸው እውቀቱ፣ ታላላቅ ያለም መሪዎችን የማሳመን ጥበቡ፣ አለ አይደል እንዲህ የመሳሰሉ ምናምን አይነት ነገሮችን ይዟቸው ነው ላይመለስ የሄደው፡፡ ባለፈው ተጠባባቂ ሚንስትሩ ራሳቸው ሲናገሩ መለስን መተካት ከባድ ነው ብለዋል፤ ታዲያ በዚህ አካሄዳቸው . . .”

“እኔም እንዲያ ነው ሚመስለኝ” አሉ ማሚቴ ንግግሬ ላይ ተደርበው፣ ቀጠሉናም “አሁን ማን ይሙት እኚህ አዲሱ መሪ እንደመለስ ይመራሉ ብላችሁ ነው? . . . እንጃ! በዚያ ላይ ሃይማኖታቸው ቤንጤ ነው መንጤ ነው አሉ ” አሉ ወደ ጋሼ ወላ በይቅርታ እይታ እያዩ፣

ወላ ፈጥነው፣ “ምነካሽ ማሚቴ ሃይማኖት የግል ነው፤ ሀገር የጋራ ነው ሲባል አልሰማሽም እንዴ? የሰውን ልክና ማንነትማ በሃይማኖቱ ልንለካውና ልንመዝነው አንችልም፡፡  ሃይማኖት ሃገር መምራትን አያግድም፤ አግዶም አያውቅም፤ ሃገር የምትመራው በዕውቀትና በጥበብ እንጂ በሃይማኖት አይደለም፣ አይደለም እንዴ ወገኖቼ?” ወላ አይኖቻቸውን በአግዙኝ አይነት ነገር አንከራተቷቸው፤

“በርግጥ እውነት ነው አገር በዕውቀትና በጥበብ እንጂ በሃይማኖት  አትመራም፣ እንዲያውም፣ መሪዎች ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረባቸው ከሆኑ፣ ህዝባቸውን በቅንነትና ታማኝነት ለመምራት ያግዛቸዋል፣ ግን . . .” ስል ሐጂ አቋረጡኝና፣

“ትክክል ብለሃል! እኛንኮ ለዘመናት የጎዱን ባንደበታቸው ፈጣሪን እናውቃለን እያሉ በሥራቸው የካዱት መሪዎች ናቸው” አሉ

“ለነገሩ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ነው፤ አገሪቱንና ህዝባቸውን በትክክል ይምሩ እንጂ አይደለም የድንግልን ልጅ መድኃኒዓለምን፣ ለምን ሳጥናኤልን አያመልኩም እኔ ምንተዳኝ?” አሉ ማሚቴ

“ዋናው ነገር ግን የመለስ ኮምፓስ ያልከው ነገር ነው፣ አሁንም ላረጋግጥልህ የምፈልገው መለስ ከነኮምፓሱ አልተቀበረም፤ አንተ እንዳልከው ከነኮምፓሱ ቢቀበርም እንኳ ይህቺን አገር ሊመራ የሚችል ሌላ ኮምፓስ ያለው ሰው አለ ብዬ በአስር ጣቶቼ ልፈርምልህ እችላለሁ፡፡” አለ ገብሩ በወኔ ተሞልቶ፤

“እኮ ያ ሰው ማነው? . . . የታለ? . . . ነው ጥያቄዬ”

“ምን አቻኮለህ፣ ጊዜው ሲደርስ ታየው የለም ወይ”

“ይሁና፣ ሁሉንም ጥያቄ ጊዜ ይመልሰዋል”

“ማነህ የኔ ልጅ አንድ ነገር ልንገርህ?” አሉኝ ሐጂ

“እሺ”

“ በነገሩ ሁሉ ጥሩ የሆነ ሰው፣ አላህን የሚፈራና በትዛዛቱ የሚኖር መሪ፣ አላህ አዲስ ኮፓስ ነው ምንድነው ያልከውን መመሪያ ያወርድለታል፤ ለምሳሌ የጥንት መሪዎቻችን ዘመናዊ ትምህርት አልነበራቸውም፡፡ ነገር ግን ከፋም ለማም አገሪቱን ሲመሩ ቆይተዋል፡፡ ዋናው የሸይጣንን ሥራ አለመስራት፣ በሰው ላይ ግፍ አለመዋል ነው፣ ደሞ ለደግ መሪ እስላሙም ክርስቲያኑም ዱአና ጸሎት ስለሚያረግለት መንግሥቱ ትጸናለታለች፣ ሰላሙ በውስጥም በውጪም ይበዛለታል ፣ አይመስልዎትም መምሬ?” አሉ ሐጂ አሻግረው በቁጨታቸው ወደተጠመዱት መምሬ አሻግሬ፣

“ልክ ነው! ሰው እግዚሐርን ከፈራና በትዛዛቶቹም ከሄደ የሚሰራው ሁሉ ይከናወንለታል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያየን እንደሆነ ንጉሥ ዳዊት ረጅም ዘመን እሥራኤልን ያስተዳደረው ፍጹም ሆኖ አንዳችም በደል ሳይገኝበት ቀርቶ ነው? . . . አይደለም፡፡ ይልቁንስ እስኪገርመን ድረስ ንጉሥ ዳዊት ኃጢያቶቹ ወሰንልክ አልነበራቸውም፡፡ ከሰው ሚስትጋ አመንዝሮ፣ ባሏን አስገድሎ፣ ድርብርብ ኃጢአት ሠርቶ እንኳ እግዚአብሔር አምላክ እንደልቤ ያለው ሰው ነው፡፡ ለምን እንዲህ አለው? ብትሉኝ፣ ንጉሥ ዳዊት ኃጢአት ሠርቶ ከኃጢአቱ ፈጥኖ በመመለስና በመጸጸት ንስኃ የሚገባ ልብ ስለነበረው፣ በላዩ ላይ አመድ ነስንሶ ወዮ እግዚአብሔር እኔ ኃጢአተኛና ወራዳ ሰው ነኝና ማረኝ እያለ ስለሚያለቅስ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ያሉ ሰዎችን ይፈልጋል፡፡ ኃጢአቱን አምኖ የሚጸጸት፣ ባደባባይ ይህን አድርጌያለሁና ይቅር በለኝ ብሎ ባልንጀራውንም ሆነ ፈጣሪውን የሚማጸን ልብ፡፡ ስለዚህ፣ መሪ ህዝቡን ካከበረና የህዝቡን የልብ ትርታ ካደመጠለት በቃ ህዝቡ ምን ይፈልጋል፤ ምንም፡፡ ግና ህዝቡን ከናቀና የግሉን ጥቅም ብቻ የሚያሳድድ ከሆነ፣ የህዝቡ ልብ ይሸፍታል፤ ባይሸፍት እንኳ ዝምታው ጡር አለው፡፡ ጦርና ጋሻ ለሌለው ንጹህ ህዝብ ደግሞ ድብቅ ጦሩ አምላኩ ነው፡፡ እንግዲህ እግዚሐር አገራችንን ይባርክልን፣ ሰላሙን ያውርድልን፣ ከውስጥና የውጪ ጠላት ይሰውርልን፣ እንቅልፍ ከማያስተኛ የጎረቤት ምቀኛ ይሰውረን!” ብለው መምሩ ሲያሳርጉ

ሁላችንም “አሜን!” አልን።ነፃነት ለኢትዮጵያ፣ፍትህ እንሻለብ ሁሌም።የፖለቲካ እሰረኞች ይፈቱ።ልማት ቢኖርም ሰበአዊ መብት ይከበር።ንፁሃን ይፈቱ።ኢህአዴግ ይብቃህ ጭቆና።የሁል ጉ ጊዜ ፀሎቴ ነው።

ማአከለ ክምችት | This entry was posted in ጉዳዮች - Affairs and tagged , , , . Bookmark the permalink.

5 Responses to የአቶ መለስ “ኮምፓስ” . . . የቡና ላይ ወግ . . . (ቶማስ ስብስቤ)

 1. Selomie Legesse ይላሉ:

  እኔም ከእናንተ ጋር “አሜን” ብያለሁ፡፡

  Like

 2. Hanibal ይላሉ:

  Tikit propoganda bite timeslalech. Lenegeru merin yemifetrew hizb new. Metsihaf ‘Wede ine betimelesu inde libe yehonu iregnochin isetachihulehu’ yilal. Inas ye Ethiopia hizb yet new yalehew?

  Like

 3. zelalemawi ይላሉ:

  አሃሃ… የቡና ላይ ወጓን ወደድኳት:: ልጅ እያለሁ አያቴ ጎረቤቶቻችንን እነ እማማ ድንቂቱን, አባባ ጨርቆን, ጋሽ ደበላን, የሥላሰ እናትን, የገረንቼል አባትን, አባባ ገብሬን ጥራ ተብዬ ተጠርተው ሲመጡ የነበረውን የቡና ላይ ወግ አስታወሰኝ… የምር! አንተ ልብ ወለድ የቡና ላይ ወግ ስታነሳ እኔን ወደልጅነት ዘመኔ መለስከኝ:: በዚያ የቡና ላይ ወግ ታዲያ የሚነሱ ወጎች ዛሬም አንዳንዶቹ ትዝ ይሉኛል… ጎረቤቶቻችን ከተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ ነበሩና የአሳብ ልዩነቱም እንደዚያው የሰፋ ነበር…ዘመኑ ደርግ ስልጣን ላይ ወጥቶ “ቀይ ሽብር ይፋፋም” ያለበት ዘመን ነበር::

  ለማንኛውም የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ “ኮምፓስ” ብለህ የሰየምከው ተስማምቶኛል:: ጃል በርታ!

  አገራችንን ኢትዮጵያን, ህዝቧንና መሪዎቿን ይባርካቸው! እግዚአብሔር አምላክ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስፈልገውን መለስ ዜናዊን የሚተካ መሪ ያመጣልን ዘንድ ጸሎቴ ነው::

  Like

 4. ያለስም ይላሉ:

  bemeles mot libe biseberim be ato hailemariyam desaleng libe metsinanatni teya yizowl b/c geta yemelesin raiyi beteshale huneta besu mesirat jemirowalina.Ye Ethiopia hizb hoye tetsinana.

  Like

 5. ያለስም ይላሉ:

  ወይ ጉድ !!!

  Like

Any comment - አስተያየት ካለዎ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s